የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ለ10ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ኮንፈረንስ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ፡፡
ኮንፈረንሱን አስመልክተው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር ) እንደተናገሩት የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎት ኮንፈረንስ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን አገራት ኮንፈረንሱን ለማዘጋጀት በሚኖራቸው ዝግጁነት ደረጃ እየተወዳደሩ የሚያዘጋጁት በመሆኑ ኢትዮጵያም በ9ኛ ዙር በዚምባብዌ በተካሄደው ኮንፈረንስ ተወዳድራ የወሰደችው ተራ ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የመንግስት አገልግሎት ኮንፈረንስ አንዱ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ነው ሁለተኛው በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ቀጠናዊ ፎረም በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ኢኖቬሽን በሚል የሚካሄድ ፎረም ነው፡፡
የመንግስት ተቋማት ተለዋዋጭ ከባቢያዊ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙና ተንከባለው የመጡ ለብዙ ጊዜ የተከማቹና ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች በፍጥነት ስለመቅረፍ ትኩረት የሚያደርግ ኮንፈረንስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዋናው የኮንፈረንሱ ዓላማ በአፍሪካ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮች በመፍታት አካታች ፣ ዘላቂ ልማት የሚያመጣ ፣ ተጠያቂነት የሚያሰፍን ፣ የሰብዓዊ መብት የሚያከብር፣ የህዝቦች ትስስር የሚያጠናክር ከባቢያዊ ሁኔታ ለመፍጠር የጠንካራ ተቋም አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑ ላይ መወያየትና መግባባት፤
እንዲሁም አፍሪካ የተከማቹ ችግሮቿን ለመፍታትና የመጪውን ጊዜ ያለመ ተልዕኮ ለመፈጸም ጠንካራ የሰው ኃብትና የመንግስት አስተዳደር የሚያስፈልጋት በመሆኑ በዚህ እና በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመረጃ ተደራሽነትና ተጠያቂነት ማስፈን አስፈላጊ በመሆኑ ላይ መወያየትና ተሞክሮ መቀያየር የጋራ መግባባት በመፍጠር ወደ የተግባር ዕቅድ መቀየር የሚያሰችሉ ሥራዎች በተመለከተ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል ኮንፈረንስ እንደሚካሄድ አክለው ገልፀዋል፡፡
ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር የባለሚናዎችና የህዝባዊ አደረጃጀት ተሳትፎዎች ማጠናከር ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ለመገንዘብ ፣የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ችግሮቻቸውን በመፍታት ያካበቱትን መልካም ልምድ መቀያየርና መማማር እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ እና፣
ፈጠራ በታከለበት አግባብ ሰው - ተኮር አገልግሎት ስለሚቀርብበት ሁኔታ ለመነጋገር፣ የአፍሪካ አገራት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚያስችል አቅም የሚገነባበት ስትራቴጂ ለመንደፍ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዬች በኮፍረሱ እንደሚካሄዱ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
አክለውም ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የሚዘዋወሩ ከሰራተኛ ቅነሳ ጋር የተያያዙ ሀሰተኛ መረጃዎች እንደሆኑ ገልፀው በዚህ አሁን መንግስት በጀመረው ሪፎርም የመንግስት ሰራተኛውን የማብቃት ፣የማዘመን አገር የመለወጥ አጀንዳ እንጂ የመንግስት ሰራተኛውን የሚያፈናቅል አንድም አዋጅ፣ ፖሊሲም ሆነ ፍኖተ ካርታ በየትኛውም ገፅ ላይ እንዳልተፀፈ ይህንንም ማንም ሰው ማየት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሰራተኛው ከእንዲህ ካለ አሉባልታ ራሱን ቆጥቦ የተጀመረው ሪፎርም እንዲሰካ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በተለይ የመንግስት ሰራተኛው ላይ ያለው ጫና በበቂ ሁኔታ ችግሩን እንደሚረዱት ገልፀው ይህን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ከሪፎርሙ ጋር በተያያዘ አጀንዳ አድርጎ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኮፈረንሱ ከሰኔ 14 እስከ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች ለ3 ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል፡፡