{jcomments on}የተቀናጀ የሲ.ሰ. መረጃ አያያዝ ስርዓት(ICSMIS)

  መግቢያ

  የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ምርትን ለማሳደግ፣ ፣ውጣ ውረድን ለመቀነስ ጊዜ ጉልበትና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ የተንዛዛ አሰራርን ለማሳጠር፣ ለቀልጣፋና ፈጣን የመረጃ ልውውጥና ስልጠት የስራ አፈፃፀም ውጤትን ለማሻሻል በአጠቃላይ የሰው ልጅን ኑሮና ህይወት ለማሻሻል መንስዔ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ህልውና የተመሰረተው በደንበኞቻቸው ፍላጎት ላይ በመሆኑ እነዚህ ተቋማት የመረጃ አያያዝ፣ አደረጃጀትና ልውውጥ በአጠቃላይ ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና ሲባል ቴክኖሎጂውን መጠቀም ደንበኞች ሳይጉላሉ በአካባቢያቸውና በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግና የአገልግሎታቸውን ጥራትና ተደራሽነት በአጠቃላይ አሰራራቸውን ማሻሻል የግድ ሆኗል፡፡ በዚህ ነባራዊ ሁኔታ አሁን አሁን በሃገራችን ያሉ የባንክ ፤ የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ሰጪ፣ የታክስና ግብር ሰብሳቢ፣ የገበያ መረጃ ሰጪ፣ የስልክ ውሃና መብራት ክፍያ ሰብሳቢ ወዘተ ተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉና አሰራራቸውን ያሻሻሉ ተቋማት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የተቀናጀ የሲ.ሰ መረጃ አያያዝ ስርዓትም የሰው ሃብት መረጃን በኤሌክትሮኒከስ ዳታ ቤዝ በማደራጀትና በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ፈጣን እንዲሆን በአጠቃላይ የዜጋውን እርካታ ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማገዝ ታስቦ እየተተገበረ ያለ ስርዓትና አንዱ የሲ.ሰ. ሪፎርም አካል ነው፡፡

  1. አሁን ያለው የመረጃ አያያዝ ሁኔታ

 በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የመረጃ አያያዝ ይህን ያህል ኃላቀር ነው ባይባልም ነገር ግን ከቴክኖሎጂ ማደግና ከመረጃ አስፈላጊነትና ቀልጣፋ አግልግሎት ከመስጠት አኳያ ሲታይ የመረጃ አያያዙ ውስብስብና አድካሚ የሆነና በሰዎች ጉልበት የሚከናወን ነው፡፡ አሁን በፌዴራል ደረጃ በስራ ላይ የሚገኘው ቋሚ የመንግስት ሰራተኞች ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ብዛት ከ107,002 በላይ ነው፡፡ ፋይላቸውም በሪከርድና ማህደር ክፍል በመዝገብ ቤት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት የለቀቁ ሰራተኞች የሚንቀሳቀስ እና ከፊል የሚንቀሳቀሱ ማህደሮችና ፋይሎች ብዛት 267,853 ይሆናል፤ ከ 1954 ዓ.ም ጀምሮ  ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነገር ግን መሰረታዊ መረጃው መጥፋት የሌለበት ከጊዜያዊ ቋሚና ጠቅላላ ጉዳይ ፋይሎች ብዛት 7,126 በላይ ይሆናሉ፡፡ በተለያየ ጊዜ የወጡ አዋጆች፣ ደንቦች መመሪያዎችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ መረጃዎች በወረቀት ማህደር ተዘጋጅቶላቸው በመደርደርያ ተቀምጠዋል፡፡ ለአንድ ጉዳይ ይሄ ፋይል ሲፈለግ በሰው ሃይል የሚፈለግ እንጂ  ራሱን የቻለ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስርዓት የለውም፡፡ ይህም ስራውን ውስብስባና አስቸጋሪ የመረጃ አደረጃጀት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከ 1955 ዓ.ም  ጀምሮ በተወሰነ መልኩ  የሰራተኛው ብዛት በፆታ፤ በትምህርት ደረጃ በቅጥር፤ የስራ መደብ ወዘተ  ስታቲስቲክስ ተይዟል፡፡ ከዚህም ባለፈ በዳታ ቤዝ ደረጃ የተጠናከረ የመረጃ አያያዝና አደረጃጀት የለም ማለት ይቻላል፡፡

 

  1. የተቀናጀ የሲ.ሰ መረጃ አያያዝ ስርዓት

የተቀናጀ የሲ.ሰ መረጃ አያያዝ ስርዓት( Integrated Civil Service Management Information System/ICSMIS) 5 ዋና ዋና ክፍሎች(ሞጁሎች) ሲኖሩት እነርሱም

  1.  የሰው ሃብት መረጃ ሞጁል፤ በአጠቃላይ የተቋመትን መዋቅር፣ የስራ ክፍሎች፣ የሰራተኞች ዝርዝር፣ የስራ መደብ፣ ደረጃ፣ የትውልድና የቅጥር ሁኔታ እና ተመሳሳይ መረጃዎችን የያዘ ሆኖ መረጃው በተፈለገ ጊዜ ከኣንድ በላይ የሆኑ ፍቃድ ያላቸው ባለሞያዎችም ጭምር በተመሳሳይ ጊዜ ለማግኘት የሚያስችል ቋት ነው
  2.  የሪከርድና ማህደር መረጃ ሞጁል፤ አሁን ያለውን የማይንቀሳቀስ፣ ከፊል የሚንቀሳቀስና ተንቀሳቃሽ ማህደሮችና ፋይሎች የግለሰብ፣ የተቋምና የጉዳይ ሊሆኑ ይችላል፤ የሚገኙበትን የመደርደሪያ ቁጥር፤ ያሉበት ሁኔታ፤ የመዝገብ ኣይነትና ቁጥር፤ መሰረታዊ መረጃ(ሜታ ዳታ) የሚይዝና በተደጋጋሚ የሚፈለጉ ሰነዶች፣ መመሪዎችና አዋጆች በተጨማሪም የህይወት ታሪክና የቅጥር ፎርሞች፤ የትምህርት ማስረጃዎች ወዘተ ስካን ተደርገው ሶፍት ኮፒያቸው የሚጫኑበት በመሆኑ ሲፈለጉ ወዲያውኑ አትሞ ለማውጣት የሚያስቻል ሲንቀሳቀሱም የተዘዋወሩበትን ክፍል የሚጠቁም ነው
  3. የአስተዳደር ፍርድ ቤት ሞጁል፤ ሰራታኛው ያለውን ቅሬታ ለማቅረብ ቀጠሮ ለማስያዝ የተሰጠውን ውሳኔ ላማወቅ ወዘተ ባለጉዳዩ በአቅራቢያው ጉዳዩን ለመከታተል የሚያስችል ዘዴ ነውየኢንስፔክሽን ሞጁል፤ የቅጥር፣ የደረጃ እድገት፣ ዝውውር ወዘተ ሁኔታን በሚፈፀምበት ወቅት ያላግባብ እንዳይሆን ለመከታተል ትክክለኛ ያልሆነ አሰራር ከመፈፀሙ በፊት በቅድሚ ለመቆጣጠር የሚረዳ ዘዴ ነው
  4. የመዋቅር   ሞጁል፤ ይህ  ሲስተም ተቋማትን ለመመዝብ፣ መዋቅር ለመትከል፣ የደመወዝ ስኬልና የሥራ መደብ ለማስገባትና የመሳሰሉትን ሥራዎች ለማከናወን ያግዛል፡፡ የመ/ቤት ዝርዝር፣ የመዋቅር ዝርዝር፣ የደመወዝ ስኬልና  ተመሳሳይ መረጃ የያዘ ክፍል ነው
  5. በተጨማሪም ፖርታል ሲኖረው፤ የተፈቀደላቸውና በሲስተሙ የተካተቱ ተጠቃሚዎች ወደ ዳታ ቤዙ በመግባት የተከናወኑ ልዩ ልዩ ወቅታዊ ጉዳዮችን ስብሰባዎች፣ የምክክር መድረኮች የበዓላት አከባበር ስነ ስርዓቶች ወዘተ በፅሁፍ፤ በፎቶግራፍና በቪድዮ የተደገፈ መረጃ ለማስቀመጥና ለማሳየት የሚያስችል ገፅታ ሲኖረው በተጨማሪም የአመት ፍቃድ ለመጠየቅና ለመፍቀድ፤ ክፍት የስራ ቦታ እንዲሞላ ለመጠየቅና ለመፍቀድ የሚረዳ የዳታ ቤዙ ዋና የመግቢያ በር ነው፡፡
  1. ማጠቃለያ

የተቀናጀ የሲ.ሰ መረጃ አያያዝ ስርዓት የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የመረጃ አያያዝ በተማከለ ቦታ እንዲቀመጥ ዳታ ማዕከል የሚገነባለት ሲሆን በስርዓቱ የሚካተቱ ተቋማት ልክ እንደ አንድ ተቋም ከላይ የተጠቀሱትን መረጃዎች ለመያዝ፣ በአግባቡ ለማደራጀትና በተፈለጉ ጊዜ ወድያውኑ ለማግኘትና በሪፖርት መልክ ለማቅረብ የሚረዳ ሲሆን ለአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና መሻሻል የበኩሉን ሁነኛ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ በትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመንደፍ፤ ለእቅድና ሪፖርት ዝግጅት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር እንደሚውልም አያጠያይቅም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሶፍትዌርና ዳታ ቤዝ የማልማት ስራ ተከናውኗል፡፡ የፕሮጀክት ፅ/ቤት ተቋቁሞ በሰው ሃይል እየተደራጀ ነው፡፡ የተጠቃሚዎች የአጠቃቀም፤ የባለሞያዎች ቴክኒካል ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በፓይለት ደረጃ 8 ሴክተሮች ተካተው ከወረዳ ኔት የማገናኘት፤ የዳታ ማዕከል ግንባታ፤ የኔት ወርክ ዕቃዎች ግዢ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ 425 የፌዴራልና የክልል ተቋማት በስርዓቱ እንደሚካተቱ የታቀደ ሲሆን በሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት በአገልግሎት አሠጣጥ ረገድ የዜጋውን ርካታ ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ሁሉም አካላት የበኩሉን ድርሻ እንዲሚወጣ ይጠበቃል፡፡

የውይይት መድረክ

የክስተቶች ካላንደር

JEvents - Legend Module

በቅርቡ የሚደረጉ ክስተቶች

No events

JEvents - Custom Module